22ኛው አለም አቀፍ የፀረ-ሙስና ቀን "ትውልድን በስነ-ምግባር ተቋምን በአሰራር" በሚል መሪ ቃል በማእከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በወልቂጤ ክላስተርበተለያዩ ሁነቶች ተከብሯል።
ሙስናን የሚከላከልና በስነ-ምግባር የታነፀ ትውልድ ማፍራት እንደሚገባ ተገለፀ ።
22ኛው አለም አቀፍ የፀረ-ሙስና ቀን "ትውልድን በስነ-ምግባር ተቋምን በአሰራር" በሚል መሪ ቃል በማእከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በወልቂጤ ክላስተርበተለያዩ ሁነቶች ተከብሯል።
የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ትራንስፖርትና መንገድ ልማት ቢሮ ምክትልና የመሠረተ ልማት ክላስተር ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት ኃላፊና የክላስተሩ አስተባባሪ ተወካይ አቶ አማን ኑረዲ እንደገለፁት ሙስና ከድህነት እና ስራ አጥነት ቀጥሎ የኢትዮጵያ ትልቁ ፈተና መሆኑን ጠቁመዋል።
ኢትዮጵያ በሁሉም ዘርፍ የጀመረችውን የእድገት ጉዞ በማስቀጠልና በ ሁለትሺ አርባ አመተ ምህረት ለመድረስ የተቀመጠው የልማት ግብ ለማሳካት ሙስናን መታገልና ማጥፋት ሲቻል እንደሆነ አቶ አማን አስገንዝበዋል።አቶ አማን አክለውም ሙስናን በዘላቂነት ለመከላከልና ለማጥፋት ትውልድ ላይ መስራት ወሳኝ ከመሆኑም በላይ ከቤተሰብ ጀምሮ እስከ ሃይማኖታዊ ተቋማት የድርሻቸውን ሊወጡ እንደሚገባ አሳስበዋል።
የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ሥራ ዕድል ፈጠራና ኢንተርፕራይዝ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ሙስጠፋ ኢሳ ሐገር የሚገነባው በትውልድ ቅብብሎሽ በመሆኑ የሐገር እድገት ፀር የሆነውን ሙስናን የመከላከልና የመዋጋት ጉዳይ የሐገር ህልውና ጉዳይ ስለሆነ ትውልድን በስነ-ምግባር ማነፅ ቅድሚያ የሚሰጠው ተግባር ነው ብለዋል።
ተቋምን በአሰራር ማዘመን ማለት ጠንካራ የሆኑ ተቋም በመገንባት ሙስናን ሌብነትን በማጥፋት አንዱ የሐገረ መንግስት ግንባታ መሰረት እንደሆነ ጠቁመዋል ።ማእከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ከተመሠረተ ጊዜ ጀምሮ ሙስናን ለመከላከል ሰፊ ስራዎች ሲሰሩ መቆየታቸው ገልፀው አሁንም ለሙስና ተጋላጭ የሆኑ የመንግስት ተቋማት የአገልግሎት አሰጣጣቸው ላይ ቆም ብለው ማየት አለባቸው ሲሉ አቶ ሙስጠፋ አሳስበዋል።
የክልሉ ስነ-ምግባርና ፀረ-ሙስና ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር አቶ ፋሲካ ጌታቸው ሙስና በተመለከተ የሚወጡ ጥናቶች እንደሚጠቀቅሙት ከሆነ እንደ ሐገር ያለንበት ደረጃ በከፍተኛ ሁኔታ መከላከል እንዳለብን የሚያሳይ ነው ሲሉ ተናግረዋል።አቶ ፋሲካ አክለውም የክልሉ የሥነ-ምግባርና ፀረ-ሙስና ኮሚሽን የግንዛቤ ማስጨበጥ ስራ ከመስጠት ጎን ለጎን በደረሱት ጥቆማ መሠረት ከ6 መቶ ሰማንያ ሶስት ሚሊዮን ብር በላይ ማስመለስና ከሙስና ማዳን መቻሉን ጠቁመው ሙስና የሚፈፀምበት መንገድ በባህሪው ተለዋዋጭ በመሆኑ ሁሉም ባለድርሻ አካላት ተሳትፎና ርብርብ እንደሚጠይቅ ገልፀዋል።
የመድረኩ ተሳታፊዎች በሰጡት አስተያየት ሙስና መከላከል ካልተቻለ እንደሐገር የተያዙት የልማት ተስፋዎች ከማስተጓገል ባለፈ እሰከ ማስቆምና ሐገር ማፍረስ ደረጃ ሊደርስ ይችላል ብለዋል።በአጥፊዎች ላይ ተገቢና ተመጣጣኝ እርምጃ በመወሰድ ሌላው እንዲማርበት ማድረግ የሙስና ተጋላጭነት መቀነስና ተቋምን ለመገንባት የአሰራር መመሪያ በማክበርና በማስከበር ውስን የህዝብና የመንግስተ ሐብት ለታለመለት ልማት ላይ ማዋል እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።
ያደጉ ሀገሮች መሠረታቸው በስነ-ምግባር የታነፀ ትውልድ ማፍራት መቻላቸው በመሆኑ እኛም ሙስናን የሚጠየፍ ትውልድ ለመቅረፅ እያንዳንዳችን ሃላፊነት አለብን ሲሉ ገልፀዋል።
ወልቂጤ , ኢትዮጵያ
011 365 9189