Skip to main content

የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ስራ ዕድል ፈጠራና ኢንተርፕራይዝ ልማት ቢሮ ከክልሉ የምግብ ስረዓት ማጠናከሪያ ፕሮግራም ጋር በመተባበር የቡድን ኢንተርፕራይዞችን አፈፃፀም ለመገምገም እና ለወረዳና ለቀበሌ ባለሙያዎች ስልጠና ለመስጠት የተዘጋጀ መድረክ በቡታጅራ ከተማ እየተካሄደ ነው።

በጠንካራ ቅንጅትና ትብብር፣ ስራ አጥነትን መቀነስ እንደሚገባ ተመላከተ

(ወልቂጤ፣ ታህሳስ 21/2018)፣ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ስራ ዕድል ፈጠራና ኢንተርፕራይዝ ልማት ቢሮ ከክልሉ የምግብ ስረዓት ማጠናከሪያ ፕሮግራም ጋር በመተባበር የቡድን ኢንተርፕራይዞችን አፈፃፀም ለመገምገም እና ለወረዳና ለቀበሌ ባለሙያዎች ስልጠና ለመስጠት የተዘጋጀ መድረክ በቡታጅራ ከተማ እየተካሄደ ነው።

የክልሉ ስራ ዕድል ፈጠራና ኢንተርፕራይዝ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ሙስጠፋ ኢሳ በዚሁ ወቅት ባደረጉት ንግግር፣ ስራ አጥነትን ደረጃ በደረጃ በመቀነስ ምርታማነትን ለማሳደግ እየተሰራ ነው ብለዋል።

በክልሉ ያሉትን እምቅ ሀብቶችንና ፀጋዎችን ለይቶ በእውቀትና በክህሎት በመመራት ወደ ሀብት በመቀየር አስተማማኝና ዘላቂ የስራ ዕድል ለመፍጠር በትኩረት እየተሰራ ነው ሲሉም ገልፀዋል።በበጀት አመቱ ለ400 ሺህ ዜጎች የስራ ዕድል ለመፍጠር እየተሰራ መሆኑን ያነሱት የቢሮ ኃላፊው፣ ከተለያዩ የክልል ተቋማት ጋር በመቀናጀት ለዘላቂ የስራ ዕድል ለመፍጠር እየተሰራ መሆኑንም ጠቁመዋል።በተለይም ከግብርና ቢሮ ጋር በመቀናጀት በገጠር ስራ ዕድል ፈጠራ የተሰማሩ ኢንተርፕራይዞችን ተጠቃሚነት ለማሳደግና የተሻለ የቴክኖሎጂ አጠቃቀም ባህል እንዲያጎለብቱ እየተሰራ ይገኛልም ብለዋል።

ተግባሩን አጠናክሮ በማስቀጠል የወጣቶቹ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነታቸው እንዲረጋገጥ እየተሰራ መሆኑንም አቶ ሙስጠፋ አመላክተዋል።የስራ ፈላጊዎችና እየተፈጠረ ያለው ስራ ተመጣጣኝ አለመሆኑን የተናገሩት የቢሮ ኃላፊው፣ ሁሉንም አማራጮች በመጠቀም በዘርፉ ያሉ መነቆዎችን መፍታት ይገባል ሲሉም ተናግረዋል።

ጠንካራ የስራ ባህል በመገንባት ሀብት ፈጠራ ላይ በማተኮር፣ ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ ገቢ ምርቶችን በመተካትና ወጪ ምርቶች ላይ አተኩሮ በመስራት ስራ አጥነትን መቅረፍ እንደሚገባም አመላክተዋል።በጠንካራ ቅንጅትና ትብብር፣ ስራ አጥነትን መቀነስ ይገባል ያሉት አቶ ሙስጠፋ፣ በግብርናው ዘርፍ የተሰማሩ ኢንተርፕራይዞች ውጤታማ እየሆኑ መምጣታቸውን ጠቁመዋል።

በክልሉ ግብርና ቢሮ የምግብ ስረዓት ማጠናከሪያ ፕሮግራም ማኔጀር አቶ ከድር መሐመድ በግብርናው የተቀረፁ ኢንሼቲቮችን ለማሳካት ፕሮግራሙ ድጋፍ እንደሚያደርግ ጠቁመዋል።ፕሮግራሙ በክልሉ ኢንተርፕራይዞች እንዲደራጁ በማገዝ፣ የፋይናንስ ድጋፍ በማድረግ እንዲሁም ኢንተርፕራይዞቹ ለሚያመርቷቸው ምርቶች የገበያ ትስስር በመፈጠር እንደሚደግፍም ተናግረዋል።

በ2017 በጀት አመት በተለያዩ የግብርና ስራዎች ለተሰማሩ 300 አባላት ያሏቸው 60 ኢንተርፕራዞች 5 ነጥብ 9 ሚሊዮን ብር ድጋፍ መደረጉንና በተያዘው በጀት አመት ደግሞ 27 ኢንተርፕራይዞችን ለመደገፍ እየተሰራ መሆኑን አብራርተዋል።የክልሉ የስራ ዕድል ፈጠራና ኢንተርፕራይዝ ልማት ቢሮ ምክትልና የገጠር ስራ ዕድል ፈጠራ ዘርፍ ኃላፊ አቶ ተመስገን ኃይሌ በበኩላቸው፣ ስራ አጥነትን ለመቅረፍ የባለድርሻ አካላት ትብብርን ይጠይቃል ብለዋል።

የወጣቱን የስራ አጥነትን ችግር ለመቅረፍ የምግብ ስረዓት ማጠናከሪያ ፕሮግራም ዘርፈ ብዙ ስራዎችን እያከናወነ እንደሚገኝ ተናግረዋል።የፕሮግራሙ ድጋፍን ውጤታማነትን ሊያረጋግጡ የሚያስችሉ የጋራ ምክክር ማድረግ ሚናው ጉልህ መሆኑንም አመላክተዋል።በመድረኩ የስራ ዕድል ፈጠራና ኢንተርፕራይዝ ልማት ቢሮ እና የግብርና ቢሮ የስራ ኃላፊዎች እንዲሁም ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።

Image